ኢየሱስ መድኃኒቴ ጌታዬ
ባንተ ነው የጣፈጠው ኑሮዬ
ስለሆንክ ባለውለታዬ
አያቋርጥም ምስጋናዬ
1. የእኔ ኢየሱስ ለኔ ልዩ ነው
ፍቅሩም እንደ ማለዳ ጠል ነው
ስጋና ደምን ዘልቶ ጅማትን
ዘልቆ ይገባል ያረካል ነፍስን
የማያቋርጥ ደስታን የሚሰጥ
መራራ ኑሮን የሚያጣፍጥ
ከኢየሱስ ዘንድ የሚመነጨው
የፍቅር ዘይት ልቤን አራሰው
2. ወረት የሌለበት ንፁህ ፍቅር
ትልቅ ትንሹን የሚያፈቅር
የሰው ማንነት ከቶ የማይገደው
ቸሩ ኢየሱስ ሰፊ ሆድ አለው
ትልቁን እንደ ትልቅነቱ
ትንሹን እንደ ትንሽነቱ
ሁሉንም ያቅፋል ከነኮተቱ
አይገመትም ጥልቀት ስፋቱ
3. ምንም እንኳን ባልሄድ በመንገዱ
ባልከተልም ፍፁም ፍቃዱ
በእኔ በልጁ ሆዱ አይጨክንም
ገፍቶ ከቤቱ አያስወጣኝም
ቢቀጣኝ እንኳን በኃጢያቴ
ሆዱ ይራራልኛል አባቴ
ልጄ እያለ ያባብለኛል
ወደ እቅፋ ይመልሰኛል
4. የልቤን ትርታ የሚያዳምጥ
ልጄ እያለ የሚያቆላምጥ
ትከሻ ሰፊ አባት ነው ያለኝ
እስከ እርጅና የሚሸከመኝ
በአባቴ ላይ ሃሳቤን ጥዬ
እኖራለሁ ተቀማጥዬ
በምንም ነገር አልጨነቅም
ስለ ነገውም ምንም አላውቅም
