አንተ የምታቀላፋ ንቃ

163

ሁሉን ፍሬ ልትበላ
ትችላለህ ከእዚህ ሌላ
በለስን ግን ከበላህ
በዚያች ቀን ትሞታለህ

ሁሉ ሞልቶ እያለልህ
ጐምጅተህ ቃሌን ተላልፈህ
በሐጥያት ፀጋ የራቀህ
ተሸሸግ ፈራህ ተደበቅ

አዳም ብዬ ብጠራህ
በስፍራው አልተገኘህም
ወርደህ በክብርህ ቦታ
ወዴት ገደል ገባህ

ልጄ የት ነው ያለኸው
ልጄ የምታቀላፋው
በል ንቃ ከሞት ተነስ
ያበራልሃል ኢየሱስ

እንዲያው እየተመላለስክ
ያልኖርክበትን ስትሰብክ

ለሰዎች መስለህ የቆምክ
አንተ ግን ነህ የተራቆትክ

ቃሉን ማንበብ ትተህ
መፀለይም አቋርጠህ
በሐጥያት እየረከስክ
መቅደሴን ታፈርሳለህ

የራስህ ጉድፍ ሳታይ
የሰው ጉድፍ ስታይ
ምንነው መከታተልህ
ልጄ ይቅር ትቢትህ

ልጄ እራስህን መርምር
ውደቅ ከመስቀሉ ስር
ነቅተህ ጌታህን ጠብቅ
የጦር መሳሪያህን ታጠቅ

ክብሬን ሁሉ ተመልክተህ
ፍቅሬን አይተህ የቀመስህ
ማንነቴን የተረዳህ
ሕይወትህን ለኔ የሰጠህ

ታዛዥም ልጄ የነበርክ
ስልክህ የምትላክ
እንደልብም የሆንክ
አለምን ሁሉ የተውክ

ዛሬ ነገር ሲሳካልህ
እቅድህ ሲሞላልህ
በአለም እየባከንህ
እኔን ታሳዝናለህ

ልጄ ሆይ ተነስ ንቃ
ማንቀላፋቱ ይብቃ
መምጫዬ የዘገየው
አንተ እስክትመለስ ነው

ልጄ የምታቀላፋ
መቅረዝህም የጠፋ
በል ንቃ አሁን ተነስ
ያበራልሃል ኢየሱስ

የሆሳዕና

Leave a Comment

Scroll to Top