መስማትና አንደበት ፍፁም የተሳነኝ
ዝግትግት ያሉብኝ ሁሉ ያልሆኑልኝ
ጣቶችህ ይዳስሱኝ ህይወትን ይዝሩልኝ
ኤፋታህ በልና ሁሉን ክፈትልኝ
ጣራ ተሸንቁሮ ወርጄ ከእግርህ ስር
ኣምኜ መጣሁኝ ኃጢያቴን ልትምር
ቃልህን ሰምቼ አልጋዬን ስሸከም
ልራመድ በቃሁኝ ሲያዩኝ በመገረም
የዳዊት ልጅ ማረኝ ምህረት አውርድልኝ
ሰርጤሜዎስ የምባል ብርሃን የናፈቀኝ
ድምፄን አሰማሁ ማንም ሳያግደኝ
ና ብለህ ጠርተኸኝ ማየትን አስቻልከኝ
ጠቢባንን ብዬ ሀብቴንም ጨርሼ
እንዲያው ስንከራተት መልሼ መልሼ
ልብስህን ስነካ ሊሆን የሚበጀኝ
መዳኔ ታውቆኛል ኃይልህ ስላገዘኝ
እንደ እሾህ የሚወጋ እረፍት የማይሰጠኝ
በሰዎች መካከል ሰላም የሚነፍገኝ
ከአንተ ሌላ ወዴት ለፈውስ እሮጣለሁ
ፀጋህ ይበቃኛል በአንተ እረካለሁ
