ጌታ ባክህ ናልኝ አውጣኝ ከፈተና
በአለም ተከብቤ ወድቄያለሁና /2/
ቀና ብዬ አንተን ልጠራህ ስሞክር
ይቅርብህ ይለኛል ወደኋላ እንድቀር
ደግሞ እተውና ጌታ ጌታ እላለሁ
ትንሽ እቆይና መልሼ ወድቃለሁ
ለመምጣት ስዘጋጅ ምልክት አይና
አለም ያስረሳኛል ያባብለኝና
ዙሪያዬ በሙሉ ክርስቲያን የለበት
አሳሳች ብቻ ነው እሾህ የበዛበት
ለመኖር ስጣጣር ጌታ አንተን መርጬ
ሥጋዬን አያለሁ ከሁሉ አስበልጬ
ታዲያ እንዲህ ሆኜ እንደምን ልለፈው
ፈተናዬ ጌታ ለዚህ ነው የጨመረው
ድኛለሁ በስምህ በሐይልህ አምላኬ
ተመስገን ልበልህ ምን አለኝ ጌታዬ /2/
ለፍቅር ልገዛ በሰላም ለመኖር
ጌታ ኢየሱስ ብዬ ልኑር በእግዚአብሔር
ቅዱስ ስጋህንም ልቀበል ኢየሱሴ
የዘለዓለም ህይወት እንድታገኝ ነፍሴ
ስሰቃይ የነበር አንተን አምላክ ክጄ
ዓለምን ሰይጣንን ሥጋዬን ወድጄ
ነበርና ጌታ የጥንቱ ጉዞዬ
አሁን ግን ተመለስኩ ተመስገን ጌታዬ
ስለዚህ ያንተ ነኝ ሌላ አምላክ የለኝም
ተመስገን ልበልህ ዛሬም ለዘለአለም
አልፋና ኦሜጋ ክበር አምላካችን
ከማጥ ያወጣኸን እኛን ልጆችህን
ኩርፊያ ስድብ ስርቆት ሐሰትንም ትቼ
ልከተልህ ጌታ ሕይወቴን አፅድቼ
በንስሃ በጾም በፀሎት ታግዤ
ነው ያሸነፍኳቸው ባንተ ሃይል ተይዤ
